Tuesday, February 9, 2010

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 50

1፤ ዮሴፍም በአባቱ ፊት ወደቀ፥ በእርሱም ላይ አለቀሰ፥ ሳመውም።

2፤ ዮሴፍም ባለመድኃኒቶች አገልጋዮቹ አባቱን በሽቱ ያሹት ዘንድ አዘዘ፤ ባለመድኃኒቶችም እስራኤልን በሽቱ አሹት።

3፤ አርባ ቀንም ፈጸሙለት፤ የሽቱ መደረጊያው ወራት እንደዚሁ ይፈጸማልና፤ የግብፅም ሰዎች ሰባ ቀን አለቀሱለት።

4፤ የልቅሶውም ወራት ባለፈ ጊዜ ዮሴፍ ለፈርዖን ቤተ ሰቦች እንዲህ ብሎ ተናገረ። እኔ በፊታችሁ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ ለፈርዖን እንዲህ ብላችሁ ንገሩት።

5፤ አባቴ አምሎኛል እንዲህ ሲል። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ በቈፈርሁት መቃብር በከነዓን ምድር ከዚያ ቅበረኝ። አሁንም ወጥቼ አባቴን ልቅበርና ልመለስ።

6፤ ፈርዖንም። ውጣ፥ አባትህንም እንዳማለህ ቅበረው አለው።

7፤ ዮሴፍም አባቱን ሊቀብር ወጣ፤ የፈርዖን ሎላልትም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወጡ፥ የቤቱ ሽማግሌዎችም የግብፅ ምድር ሽማግሌዎችም ሁሉ፤

8፤ የዮሴፍም ቤተ ሰቦች ሁሉ ወንድሞቹም የአባቱም ቤተ ሰቦች ወጡ፤ ልጆቻቸውንና በጎቻቸውን ከብቶቻቸውን ብቻ በጌሤም ተዉ።

9፤ ሰረገሎችም ፈረሰኞችም ከእርሱ ጋር ወጡ፥ ሠራዊቱም እጅግ ብዙ ነበረ።

10፤ በዮርዳኖስ ማዶ ወዳለችው ወደ አጣድ አውድማ መጡ፥ እጅግ ታላቅ በሆነ በጽኑ ልቅሶም አለቀሱለት፤ ለአባቱም ሰባት ቀን ልቅሶ አደረገለት።

11፤ በዚያች ምድር የሚኖሩ የከነዓን ሰዎችም በአጣድ አውድማ የሆነውን ልቅሶ ባዩ ጊዜ። ይህ ለግብፅ ሰዎች ታላቅ ልቅሶ ነው አሉ፤ ስለዚህም የዚያን ቦታ ስም አቤል ምጽራይም ብለው ጠሩት፤ እርሱም በዮርዳኖስ ማዶ ነው።

12፤ ልጆቹም እንዳዘዛቸው እንደዚያው አደረጉለት፤

13፤ ልጆቹም ወደ ከነዓን ምድር አጓዙት፥ ባለ ሁለት ክፍል በሆነች ዋሻም ቀበሩት፤ እርስዋም በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት ዋሻ ናት።

14፤ ዮሴፍና ወንድሞቹ አባቱንም ሊቀብሩ ከእርሱ ጋር የወጡት ሰዎች ሁሉ አባቱን ከቀበረ በኋላ ወደ ግብፅ ተመለሱ።

15፤ የዮሴፍም ወንድሞች አባታቸው እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እንዲህ አሉ። ምናልባት ዮሴፍ ይጠላን ይሆናል፥ ባደረግንበትም ክፋት ሁሉ ብድራት ይመልስብን ይሆናል።

16፤ ወደ ዮሴፍም መልእክት ላኩ እንዲህም አሉት። አባትህ ገና ሳይሞት እንዲህ ብሎ አዝዞአል።

17፤ ዮሴፍን እንዲህ በሉት። እባክህ የወንድሞችህን በደል ኃጢአታቸውንም ይቅር በል፥ እነርሱ በአንተ ከፍተውብሃልና፤ አሁንም እባክህ የአባትህ አምላክ ባሪያዎች የበደሉህን ይቅር በል።

18፤ ዮሴፍም ይህን ሲሉት አለቀሰ። ወንድሞቹ ደግሞ መጡ በፊቱም ሰግደው። እነሆ እኛ ለአንተ ባሪያዎችህ ነን አሉት።

19፤ ዮሴፍም አላቸው። አትፍሩ፤ እኔ በእግዚአብሔር ፋንታ ነኝን?

20፤ እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ፤ እግዚአብሔር ግን ዛሬ እንደ ሆነው ብዙ ሕዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።

21፤ አሁንም አትፍሩ፤ እኔ እናንተንና ልጆቻችሁን እመግባችኋለሁ። አጽናናቸውም ደስ አሰኛቸውም።

22፤ ዮሴፍም በግብፅ ተቀመጠ፥ እርሱና የአባቱም ቤተ ሰብ፤ ዮሴፍም መቶ አሥር ዓመት ኖረ።

23፤ ዮሴፍም የኤፍሬምን ልጆች እስከ ሦስት ትውልድ አየ፤ የምናሴ ልጅ የማኪር ልጆችም በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ።

24፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አለ። እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም መጎብኘትን ይጎበኛችኋል፥ ከዚህችም ምድር ያወጣችኋል፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም ወደ ማለላቸው ምድር ያደርሳችኋል።

25፤ ዮሴፍም የእስራኤልን ልጆች። እግዚአብሔር ሲያስባችሁ አጥንቴን ከዚህ አንሥታችሁ ከእናንተ ጋር ውሰዱ ብሎ አማላቸው።

26፤ ዮሴፍም በመቶ አሥር ዓመት ዕድሜው ሞተ፤ በሽቱም አሹት፥ በግብፅ ምድር በሣጥን ውስጥ አኖሩት።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 49

1፤ ያዕቆብም ልጆቹን ጠርቶ እንዲህ አለ። በኋለኛው ዘመን የሚያገኛችሁን እንድነግራችሁ ተሰብሰቡ።

2፤ እናንት የያዕቆብ ልጆች ተሰብሰቡ፥ ስሙም፤ አባታችሁ እስራኤልንም አድምጡ።

3፤ ሮቤል፥ አንተ በኵር ልጄና ኃይሌ፥ የጕብዝናዬም መጀመሪያ ነህ፤ የክብር አለቃና የኃይል አለቃ።

4፤ እንደ ውኃ የምትዋልል ነህ፤ አለቅነት ለአንተ አይሁን፤ ወደ አባትህ መኝታ ወጥተሃልና፤ አረከስኸውም፤ ወደ አልጋዬም ወጣ።

5፤ ስምዖንና ሌዊ ወንድማማች ናቸው፤ ሰይፎቻቸው የዓመፃ መሣሪያ ናቸው።

6፤ በምክራቸው፥ ነፍሴ፥ አትግባ፤ ከጉባኤአቸውም ጋር፥ ክብሬ፥ አትተባበር፤ በቍጣቸው ሰውን ገድለዋልና፥ በገዛ ፈቃዳቸውም በሬን አስነክሰዋልና።

7፤ ቍጣቸው ርጉም ይሁን፥ ጽኑ ነበርና፤ ኵርፍታቸውም፥ ብርቱ ነበርና፤ በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ፥ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ።

8፤ ይሁዳ፥ ወንድሞችህ አንተን ያመሰግኑሃል፤ እጅህ በጠላቶችህ ደንደስ ላይ ነው፤ የአባትህ ልጆች በፊትህ ይሰግዳሉ።

9፤ ይሁዳ የአንበሳ ደቦል ነው፤ ልጄ ሆይ፥ ከአደንህ ወጣህ፤ እንደ አንበሳ አሸመቀ፥ እንደ ሴት አንበሳም አደባ፤ ያስነሣውስ ዘንድ ማን ይችላል?

10፤ በትረ መንግሥት ከይሁዳ አይጠፋም፥ የገዥም ዘንግ ከእግሮቹ መካከል፥ ገዥ የሆነው እስኪመጣ ድረስ፤ የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።

11፤ ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፥ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፥ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም።

12፤ ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል።

13፤ ዛብሎን በባሕር ዳር ይቀመጣል፤ እርሱም ለመርከቦች ወደብ ይሆናል፤ ዳርቻውም እስከ ሲዶና ድረስ ነው።

14፤ ይሳኮር አጥንተ ብርቱ አህያ ነው፥ በበጎች ጕረኖም መካከል ያርፋል።

15፤ ዕረፍትም መልካም መሆንዋን አየ፥ ምድሪቱም የለማች መሆንዋን፤ ትከሻውን ለመሸከም ዝቅ አደረገ፥ በሥራም ገበሬ ሆነ።

16፤ ዳን በወገኑ ይፈርዳል፥ ከእስራኤል ነገድ እንደ አንዱ።

17፤ ዳን በጐዳና ላይ እንደ እባብ ይሆናል፥ በመንገድም እንደ ቀንዳም እባብ፤ ፈረሱን ከሰኮናው ይነክሳል፥ ፈረሰኛም ወደ ኋላው ይወድቃል።

18፤ እግዚአብሔር ሆይ፥ መድኃኒትህን እጠብቃለሁ።

19፤ ጋድን ዘማቾች ይዘምቱበታል፤ እርሱ ግን ተከታትሎ ይዘምትባቸዋል።

20፤ የአሴር እንጀራው ወፍራም ነው፥ ለነገሥታቱም ደስ የሚያሰኝ መብልን ይሰጣል።

21፤ ንፍታሌም የተፈታ ሚዳቋ ነው፤ መልካም ቃልን ይሰጣል።

22፤ ዮሴፍ ትንሹ የፍሬ ዛፍ ነው፥ በምንጭ አጠገብ የሚያፈራ የፍሬ ዛፍ፤ አረጎቹ በቅጥር ላይ ያድጋሉ።

23፤ ቀስተኞች አስቸገሩት፥ ነደፉትም፥ ተቃወሙትም፤

24፤ ነገር ግን ቀስቱ እንደ ጸና ቀረ፤ የእጆቹም ክንድ በያዕቆብ አምላክ እጅ በረታ፥ በዚያው በጠባቂው በእስራኤል ዓምድ፥

25፤ በአባትህ አምላክ እርሱም የሚረዳህ፥ ሁሉንም በሚችል አምላክ እርሱም የሚባርክህ፥ በሰማይ በረከት ከላይ በሚገኝ፥ በጥልቅም በረከት ከታች በሚሠራጭ፥ በጡትና በማኅፀን በረከት።

26፤ የአባትህ በረከቶች ጽኑዓን ከሆኑ ከተራሮች በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ ዘላለማውያን ከሆኑ ከኮረፍቶችም በረከቶች ይልቅ ኃያላን ናቸው፤ እነርሱም በዮሴፍ ራስ ላይ ይሆናሉ፥ በወንድሞቹ መካከል አለቃ በሆነው ራስ አናት ላይ።

27፤ ብንያም ነጣቂ ተኵላ ነው፤ የበዘበዘውን በጥዋት ይበላል፥ የማረከውንም በማታ ይካፈላል።

28፤ እነዚህም ሁሉ አሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ናቸው፤ አባታቸው የነገራቸው ይህ ነው፥ ባረካቸውም፤ እያንዳንዳቸውን እንደ በረከታቸው ባረካቸው።

29፤ እንዲህ ብሎም አዘዛቸው። እኔ ወደ ወገኖቼ እሰበሰባለሁ፤ በኬጢያዊ በኤፍሮን እርሻ ላይ ባለችው ዋሻ ከአባቶቼ ጋር ቅበሩኝ፤

30፤ እርስዋም በከነዓን ምድር በመምሬ ፊት ያለች፥ አብርሃም ለመቃብር ርስት ከኬጢያዊ ከኤፍሮን ከእርሻው ጋር የገዛት፥ ባለ ድርብ ክፍል ዋሻ ናት።

31፤ አብርሃምና ሚስቱ ሣራ ከዚያ ተቀበሩ፤ ይስሐቅና ሚስቱ ርብቃ ከዚያ ተቀበሩ፤ ከዚያም እኔ ልያን ቀበርኋት፤

32፤ እርሻውና በእርስዋ ላይ ያለችው ዋሻ ከኬጢ ልጆች የተገዙ ናቸው።

33፤ ያዕቆብም ትእዛዙን ለልጆቹ ተናግሮ በፈጸመ ጊዜ እግሮቹን በአልጋው ላይ ሰብስቦ ሞተ፥ ወደ ወገኖቹም ተከማቸ።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 48

1፤ ከዚህም ነገር በኋላ እንዲህ ሆነ፤ እነሆ አባትህ ታምሞአል ብለው ለዮሴፍ ነገሩት፤ እርሱም ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ሄደ።

2፤ ለያዕቆብም። እነሆ ልጅህ ዮሴፍ መጥቶልሃል ብለው ነገሩት፤ እስራኤልም ተጠነካከረ፥ በአልጋውም ላይ ተቀመጠ።

3፤ ያዕቆብ ዮሴፍን አለው። ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር በሎዛ ተገለጠልኝ፥ ባረከኝም

4፤ እንዲህም አለኝ። እነሆ ፍሬያማ አደርግሃለሁ፥ አበዛሃለሁም፥ ለብዙም ሕዝብ ጉባኤ አደርግሃለሁ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለዘላለም ርስት ለዘርህ እሰጣታለሁ።

5፤ አሁንም እኔ ወደ አንተ ከመምጣቴ በፊት በግብፅ ምድር የተወለዱልህ ሁለቱ ልጆችህ ለእኔ ይሁኑ፤ ኤፍሬምና ምናሴ ለእኔ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ናቸው።

6፤ ከእነርሱም በኋላ የምትወልዳቸው ልጆች ለአንተ ይሁኑ፤ በርስታቸው በወንድሞቻቸው ስም ይጠሩ።

7፤ እኔም ከመስጴጦምያ በመጣሁ ጊዜ፥ ወደ ኤፍራታ ለመግባት ጥቂት ቀርቶኝ በመንገድ ሳለሁ፥ ራሔል በከነዓን ምድር ሞተችብኝ፤ በዚያም በኤፍራታ መንገድ ላይ፥ እርስዋም ቤተ ልሔም ናት፥ ቀበርኋት።

8፤ እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች አይቶ። እነዚህ እነማን ናቸው? አለው።

9፤ ዮሴፍም ለአባቱ። እግዚአብሔር በዚህ የሰጠኝ ልጆቼ ናቸው አለ። እርሱም። እባርካቸው ዘንድ ወደዚህ አቅርብልኝ አለ።

10፤ የእስራኤልም ዓይኖች ከሽምግልና የተነሣ ከብደው ነበር፥ ማየትም አይችልም ነበር፤ ወደ እርሱም አቀረባቸው፥ ሳማቸውም፥ አቀፋቸውም።

11፤ እስራኤልም ዮሴፍን። ፊትህን አያለሁ ብዬ አላሰብሁም ነበር፤ እነሆም እግዚአብሔር ዘርህን ደግሞ አሳየኝ አለው።

12፤ ዮሴፍም ከጕልበቱ ፈቀቅ አደረጋቸው፥ ወደ ምድርም በግምባሩ ሰገደ።

13፤ ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፥ ኤፍሬምንም በቀኙ በእስራኤል ግራ፥ ምናሴንም በግራው በእስራኤል ቀኝ አደረገው፥ ወደ እርሱም አቀረባቸው።

14፤ እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረው፥ እርሱም ታናሽ ነበረ፥ ግራውንም በምናሴ ራስ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ፥ ምናሴ በኵር ነበርና።

15፤ ያዕቆብም ዮሴፍን ባረከ እንዲህም አለ። አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ በፊቱ የሄዱለት እርሱ እግዚአብሔር፥ ከታናሽነቴ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እኔን የመገበኝ እግዚአብሔር፥

16፤ ከክፉ ነገር ሁሉ ያዳነኝ መልአክ፥ እርሱ እነዚህን ብላቴኖች ይባርክ፤ ስሜም የአባቶቼ የአብርሃምና የይስሐቅም ስም በእነርሱ ይጠራ፤ በምድርም መካከል ይብዙ።

17፤ ዮሴፍም አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ላይ ጭኖ ባየ ጊዜ አሳዘነው፤ የአባቱንም እጅ በምናሴ ራስ ላይ ይጭነው ዘንድ ከኤፍሬም ራስ ላይ አነሣው።

18፤ ዮሴፍም አባቱን። አባቴ ሆይ እንዲህ አይደለም፥ በኵሩ ይህ ነውና፤ ቀኝህን በራሱ ላይ አድርግ አለው።

19፤ አባቱም እንቢ አለ እንዲህ ሲል። አወቅሁ ልጄ ሆይ፥ አወቅሁ፤ ይህም ደግሞ ሕዝብ ይሆናል ታላቅም ይሆናል፤ ነገር ግን ታናሽ ወንድሙ ከእርሱ ይበልጣል፥ ዘሩም የአሕዛብ ሙላት ይሆናል።

20፤ በዚያም ቀን እንዲህ ብሎ ባረካቸው። በእናንተ እስራኤል እንዲህ ብሎ ይባርካል። እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርግህ። ኤፍሬምንም ከምናሴ ፊት አደረገው።

21፤ እስራኤልም ዮሴፍን። እነሆ እኔ እሞታለሁ፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል፥ ወደ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤

22፤ እኔም ከአሞራውያን በሰይፌና በቀስቴ የወሰድሁትን ለአንተ ከወንድሞችህ አንድ እጅ አብልጬ ሰጠሁህ አለው።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 47

1፤ ዮሴፍም ገባ ለፈርዖንም ነገረው እንዲህ ብሎ። አባቴና ወንድሞቼ በጎቻቸውም ላሞቻቸውም ያላቸውም ሁሉ ከከነዓን ምድር ወጡ፤ እነርሱም እነሆ በጌሤም ምድር ናቸው።

2፤ ከወንድሞቹም አምስት ሰዎችን ወስዶ በፈርዖን ፊት አቆማቸው።

3፤ ፈርዖንም ወንድሞቹን። ሥራችሁ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም ፈርዖንን። እኛ ባሪያዎችህ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ በግ አርቢዎች ነን አሉት።

4፤ ፈርዖንንም እንዲህ አሉት። በምድር ልንቀመጥ በእንግድነት መጣን፥ የባርያዎችህ በጎች የሚሰማሩበት ስፍራ የለምና፤ ራብ በከነዓን ምድር እጅግ ጸንቶአልና፤ አሁንም ባሪያዎችህ በጌሤም ምድር እንድንቀመጥ እንለምንሃለን።

5፤ ፈርዖንም ዮሴፍን ተናገረው እንዲህ ብሎ። አባትህና ወንድሞችህ መጥተውልሃል፤

6፤ የግብፅ ምድር በፊትህ ናት፤ በመልካሙ ምድር አባትህንና ወንድሞችህን አኑራቸው፤ በጌሤም ምድር ይኑሩ፤ ከእነርሱም ውስጥ እውቀት ያላቸውን ሰዎች ታውቅ እንደ ሆነ በእንስሶቼ ላይ አለቆች አድርጋቸው።

7፤ ዮሴፍም ያዕቆብን አባቱን አስገብቶ በፈርዖን ፊት አቆመው፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው።

8፤ ፈርዖንም ያዕቆብን። የዕድሜህ ዘመን ስንት ዓመት ነው? አለው።

9፤ ያዕቆብም ለፈርዖን አለው። የእንግድነቴ ዘመን መቶ ሠላሳ ዓመት ነው፤ የሕይወቴ ዘመኖች ጥቂትም ክፉም ሆኑብኝ፥ አባቶቼ በእንግድነት የተቀመጡበትንም ዘመን አያህሉም።

10፤ ያዕቆብም ፈርዖንን ባረከው ከፈርዖንም ፊት ወጣ።

11፤ ዮሴፍም አባቱንና ወንድሞቹን አኖረ፥ ፈርዖን እንዳዘዘም በግብፅ ምድር በተሻለችው በራምሴ ምድር ጉልትን ሰጣቸው።

12፤ ዮሴፍም ለአባቱና ለወንድሞቹ ለአባቱም ቤተ ሰዎች ሁሉ እንደ ልጆቻቸው መጠን እህል ሰጣቸው።

13፤ በምድርም ሁሉ እህል አልነበረም፥ ራብ እጅግ ጸንቶአልና፤ ከራብም የተነሣ የግብፅ ምድርና የከነዓን ምድር ተጎዳ።

14፤ ዮሴፍም ከግብፅ ምድርና ከከነዓን ምድር በእህል ሸመት የተገኘውን ብሩን ሁሉ አከማቸ፤ ዮሴፍም ብሩን ወደ ፈርዖን ቤት አስገባው።

15፤ ብሩም በግብፅ ምድርና በከነዓን ምድር አለቀ፤ የግብፅ ሰዎችም ሁሉ ወደ ዮሴፍ መጡ እንዲህ ሲሉ። እንጀራ ስጠን፤ ስለ ምን በፊትህ እንሞታለን? ብሩ አልቆብናልና።

16፤ ዮሴፍም። ከብቶቻችሁን አምጡልኝ፤ ብር ካለቀባችሁ በከብቶቻችሁ ፋንታ እህል እሰጣችኋለሁ አለ።

17፤ ከብቶቻቸውንም ወደ ዮሴፍ አመጡ፥ ዮሴፍም በፈረሶቻቸው በበጎቻቸውም በላሞቻቸውም በአህዮቻቸውም ፋንታ እህልን ሰጣቸው፤ በዚያች ዓመትም ስለ ከብቶቻቸው ሁሉ ፋንታ እህልን መገባቸው።

18፤ ዓመቱም ተፈጸመ፤ በሁለተኛውም ዓመት ወደ እርሱ መጥተው እንዲህ አሉት። እኛ ከጌታችን አንሰውርም፤ ብሩ በፍጹም አለቀ፥ ከብታችንም ከጌታችን ጋር ነው፤ ከሰውነታችንና ከምድራችን በቀር በጌታችን ፊት አንዳች የቀረ የለም፤

19፤ እኛ በፊትህ ስለ ምን እንሞታለን? ምድራችንስ ስለ ምን ትጠፋለች? እኛንም ምድራችንንም በእህል ግዛን፥ እኛም ለፈርዖን ባሪያዎች እንሁን፥ ምድራችንም ለእርሱ ትሁን፤ እኛ እንድንድን እንዳንሞትም ምድራችንም እንዳትጠፋ ዘር ስጠን።

20፤ ዮሴፍም የግብፅን ምድር ሁሉ ለፈርዖን ገዛ፥ የግብፅ ሰዎች ሁሉ ራብ ስለ ጸናባቸው ርስታቸውን ሸጠዋልና፤ ምድሪቱ ለፈርዖን ሆነች።

21፤ ሕዝቡንም ሁሉ ከግብፅ ዳርቻ አንሥቶ እስከ ሌላው ዳርቻዋ ድረስ ባሪያዎች አደረጋቸው።

22፤ የካህናትን ምድር ብቻ አልገዛም፥ ካህናቱ ከፈርዖን ዘንድ ድርጎ ያገኙ ነበርና፥ ፈርዖንም የሰጣቸውን ድርጎ ይበሉ ነበር፤ ስለዚህም ምድራቸውን አልሸጡም።

23፤ ዮሴፍም ሕዝቡን እንዲህ አለ። እነሆ ዛሬ እናንተንና ምድራችሁን ለፈርዖን ገዝቻችኋለሁ፤ ዘር ውሰዱና ምድሪቱን ዝሩ፤

24፤ በመከርም ጊዜ ፍሬውን ከአምስት እጅ አንዱን እጅ ለፈርዖን ስጡ፤ አራቱም እጅ ለእናንተ ለራሳችሁ፥ ለእርሻው ዘርና ለእናንተ ምግብ፥ ለቤተ ሰዋችሁና ለሕፃናቶቻችሁም ሲሳይ ይሁን።

25፤ እነርሱም። አንተ አዳነኸን፤ በጌታችን ፊት ሞገስን አናግኝ፥ ለፈርዖንም ባሪያዎች እንሆናለን አሉት።

26፤ ዮሴፍም ለፈርዖን ካልሆነችው ከካህናቱ ምድር በቀር አምስተኛው እጅ ለፈርዖን እንዲሆን በግብፅ ምድር እስከ ዛሬ ድረስ ሕግ አደረጋት።

27፤ እስራኤልም በግብፅ ምድር በጌሤም አገር ተቀመጠ፤ ገዙአትም፥ ረቡ፥ እጅግም በዙ።

28፤ ያዕቆብም በግብፅ ምድር አሥራ ሰባት ዓመት ተቀመጠ፤ የያዕቆብም ሙላው የሕይወቱ ዘመን መቶ አርባ ሰባት ዓመት ነው።

29፤ የእስራኤልም የሞቱ ቀን ቀረበ፤ ልጁን ዮሴፍንም ጠርቶ እንዲህ አለው። በፊትህ ሞገስን አግኝቼ እንደ ሆንሁ እጅህን ከጭኔ በታች አድርግ፥ በግብፅ ምድርም እንዳትቀብረኝ ምሕረትንና እውነትን አድርግልኝ፤

30፤ ከአባቶቼም ጋር በተኛሁ ጊዜ ከግብፅ ምድር አውጥተህ ትወስደኛለህ፥ በመቃብራቸውም ትቀብረኛለህ። እርሱም። እንደ ቃልህ አደርጋለሁ አለ።

31፤ እርሱም። ማልልኝ አለው። ዮሴፍም ማለለት፤ እስራኤልም በአልጋው ራስ ላይ ሰገደ።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 46

1፤ እስራኤልም ለእርሱ ያለውን ሁሉ ይዞ ተነሣ፥ ወደ ቤርሳቤህ መጣ፥ መሥዋዕትንም ለአባቱ ለይስሐቅ አምላክ ሠዋ።

2፤ እግዚአብሔርም በሌሊት ራእይ። ያዕቆብ ያዕቆብ ብሎ ለእስራኤል ተናገረው። እርሱም። እነሆኝ አለ።

3፤ አለውም። የአባቶችህ አምላክ እግዚአብሔር እኔ ነኝ፤ ወደ ግብፅ መውረድ አትፍራ፥ በዚያ ትልቅ ሕዝብ አደርግሃለሁና።

4፤ እኔ ወደ ግብፅ አብሬህ እወርዳለሁ፥ ከዚያም ደግሞ እኔ አወጣሃለሁ፤ ዮሴፍም እጁን በዓይንህ ላይ ያኖራል።

5፤ ያዕቆብም ከቤርሳቤህ ተነሣ፤ የእስራኤልም ልጆች ያዕቆብን ይወስዱ ዘንድ ፈርዖን በሰደዳቸው ሰረገሎች አባታቸውን ያዕቆብንና ሕፃናቶቻቸውን ሴቶቻቸውንም ወሰዱ።

6፤ እንስሶቻቸውንም በከነዓን አገርም ያገኙትን ከብታቸውን ሁሉ ይዘው ያዕቆብና ዘሩ ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ መጡ፤

7፤ ወንዶች ልጆቹንና የልጆቹን ወንዶች ልጆች፥ ሴቶች ልጆቹንና የወንዶች ልጆቹን ሴቶች ልጆች፥ ዘሩንም ሁሉ ከእርሱ ጋር ወደ ግብፅ አስገባቸው።

8፤ ወደ ግብፅም የገቡት የእስራኤል ልጆች ስም ይህ ነው፥ ያዕቆብና ልጆቹ፤ የያዕቆብ በኵር ሮቤል።

9፤ የሮቤልም ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉሶ፥ አስሮን፥ ከርሚ።

10፤ የስሞዖን ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊት ልጅ ሳኡል።

11፤ የሌዊም ልጆች፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።

12፤ የይሁዳም ልጆች፤ ዔር፥ አውናን፥ ሴሎም፥ ፋሬስ፥ ዛራ፤ ዔርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ፤ የፋሬስም ልጆች ኤስሮም፥ ሐሙል።

13፤ የይሳኮርም ልጆች፤ ቶላ፥ ፉዋ፥ ዮብ፥ ሺምሮን።

14፤ የዛብሎንም ልጆች፤ ሴሬድ፥ ኤሎን፥ ያሕልኤል።

15፤ ልያ በመስጴጦምያ በሶርያ ለያዕቆብ የወለደቻቸው ልጆችና ሴቲቱ ልጅዋ ዲና እነዚህ ናቸው፤ ወንዶችም ሴቶችም ልጆችዋ ሁሉ ሠላሳ ሦስት ነፍስ ናቸው።

16፤ የጋድም ልጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ ኤስቦን፥ ዔሪ፥ አሮዲ፥ አርኤሊ።

17፤ የአሴርም ልጆች፤ ዪምና፥ የሱዋ፥ የሱዊ፥ በሪዓ፥ እኅታቸው ሤራሕ፤ የበሪዓ ልጆችም፤ ሔቤር፥ መልኪኤል።

18፤ ላባ ለልጁ ለልያ የሰጣት የዘለፋ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህን አሥራ ስድስቱንም ነፍስ ለያዕቆብ ወለደች።

19፤ የያዕቆብ ሚስት የራሔል ልጆች ዮሴፍና ብንያም ናቸው።

20፤ ለዮሴፍም በግብፅ ምድር ምናሴና ኤፍሬም ተወለዱለት፤ የሄልዮቱ ከተማ ካህን የጶጥፌራ ልጅ አስናት የወለደቻቸው ናቸው።

21፤ የብንያምም ልጆች፤ ቤላ፥ ቤኬር፥ አስቤል፤ የቤላ ልጆችም፤ ጌራ፥ ናዕማን፥ አኪ፥ ሮስ፥ ማንፌን፥ ሑፊም፤ ጌራም አርድን ወለደ።

22፤ ለያዕቆብ የተወለዱለት የራሔልም ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ሁሉም አሥራ አራት ነፍስ ናቸው።

23፤ የዳንም ልጆች፤ ሑሺም።

24፤ የንፍታሌምም ልጆች፤ ያሕጽኤል፥ ጉኒ፥ ዬጽር፥ ሺሌም።

25፤ ላባ ለልጁ ለራሔል የሰጣት የባላ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ እነዚህንም ለያዕቆብ ወለደችለት፤ ሁሉም ሰባት ነፍስ ናቸው።

26፤ ከያዕቆብ ጋር ወደ ግብፅ የገቡት ሰዎች ሁሉ ከጉልበቱ የወጡት፥ ከልጆቹ ሚስቶች ሌላ፥ ሁላቸው ስድሳ ስድስት ናቸው።

27፤ በግብፅ ምድር የተወለዱለት የዮሴፍም ልጆች ሁለት ናቸው፤ ወደ ግብፅ የገቡት የያዕቆብ ቤተ ሰዎች ሁሉ ሰባ ናቸው።

28፤ ይሁዳንም በጌሤም እንዲቀበለው በፊቱ ወደ ዮሴፍ ላከ፤ ወደ ጌሤም ምድርም ደረሱ።

29፤ ዮሴፍም ሰረገላውን አዘጋጀ፥ አባቱንም እስራኤልን ሊገናኘው ወደ ጌሤም ወጣ፤ ባየውም ጊዜ በአንገቱ ላይ ወደቀ፥ አቅፎትም ረጅም ጊዜ አለቀሰ።

30፤ እስራኤልም ዮሴፍን። አንተ ገና በሕይወት ሳለህ ፊትህን አይቼአለሁና አሁን ልሙት አለው።

31፤ ዮሴፍም ወንድሞቹንና የአባቱን ቤተ ሰዎች እንዲህ አላቸው። እኔ መጥቼ ለፈርዖን እንዲህ ብዬ እነግረዋለሁ። በከነዓን ምድር የነበሩት ወንድሞቼና የአባቴ ቤተ ሰዎች ወደ እኔ መጥተዋል፤

32፤ እነርሱም በግ የሚጠብቁ ሰዎች ናቸው፥ እንስሳ ያረቡ ነበርና፤ በጎቻቸውንና ላሞቻቸውን ያላቸውንም ሁሉ አመጡ።

33፤ ፈርዖንም ቢጠራችሁ። ተግባራችሁስ ምንድር ነው? ቢላችሁ፥

34፤ በግ ጠባቂ ሁሉ ለግብፅ ሰዎች ርኵስ ነውና በጌሤም እንድትቀመጡ እንዲህ በሉት። እኛ ባሪያዎችህ ከብላቴናነታችን ጀምረን እስከ አሁን ድረስ፥ እኛም አባቶቻችንም፥ እንስሳ አርቢዎች ነን።

q ቍ@28፤ ጌሤም የሚለውን የግእዝ መጽሐፍ ራምሴ ይለዋል።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 45

1፤ ዮሴፍም በእርሱ ዘንድ ቆመው ባሉት ሰዎች ሁሉ ፊት ሊታገሥ አልተቻለውም። ሰዎቹንም ሁሉ ከፊቴ አስወጡልኝ ብሎ ጮኾ ተናገረ፤ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ራሱን በገለጠ ጊዜ በእርሱ ዘንድ የቆመ ማንም አልነበረም።

2፤ ቃሉንም ከፍ አድርጎ አለቀሰ፤ የግብፅ ሰዎችም ሰሙ፥ በፈርዖን ቤትም ተሰማ።

3፤ ዮሴፍም ለወንድሞቹ። እኔ ዮሴፍ ነኝ፤ አባቴ እስከ አሁን በሕይወቱ ነውን? አለ። ወንድሞቹም ይመልሱለት ዘንድ አልቻሉም፥ በፊቱ ደንግጠው ነበርና።

4፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን። ወደ እኔ ቅረቡ አለ። ወደ እርሱም ቀረቡ። እንዲህም አላቸው። ወደ ግብፅ የሸጣችሁኝ እኔ ወንድማችሁ ዮሴፍ ነኝ።

5፤ አሁንም ወደዚህ ስለ ሸጣችሁኝ አትዘኑ፥ አትቈርቈሩም፤ እግዚአብሔር ሕይወትን ለማዳን ከእናንተ በፊት ሰድዶኛልና።

6፤ ይህ ሁለቱ ዓመት በምድር ላይ ራብ የሆነበት ነውና፤ የማይታረስበትና የማይታጨድበት አምስት ዓመት ገና ቀረ።

7፤ እግዚአብሔርም በምድር ላይ ቅሬታን አስቀርላችሁ ዘንድ በታላቅ መድኃኒትም አድናችሁ ዘንድ ከእናንተ በፊት ላከኝ።

8፤ አሁንም እናንተ ወደዚህ የላካችሁኝ አይደላችሁም፥ እግዚአብሔር ላከኝ እንጂ፤ ለፈርዖንም እንደ አባት አደረገኝ፥ በቤቱም ሁሉ ላይ ጌታ፥ በግብፅ ምድርም ሁሉ ላይ አለቃ አደረገኝ።

9፤ አሁንም ፈጥናችሁ ወደ አባቴ ውጡ፥ እንዲህም በሉት። ልጅህ ዮሴፍ የሚለው ነገር ይህ ነው። እግዚአብሔር በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ጌታ አደረገኝ፤ ወደ እኔ ና፥ አትዘግይ፤

10፤ በጌሤምም ምድር ትቀመጣለህ፥ ወደ እኔም ትቀርባለህ፥ አንተና ልጆችህ የልጆችህም ልጆች፥ በጎችህና ላሞችህ ከብትህም ሁሉ።

11፤ በዚያም አንተና የቤትህ ሰዎች የአንተ የሆነው ሁሉ እንዳትቸገሩ እመግብሃለሁ የራቡ ዘመን ገና አምስት ዓመት ቀርቶአልና።

12፤ እነሆም ለእናንተ የተናገረቻችሁ የእኔ አፍ እንደ ሆነች የእናንተ ዓይኖች አይተዋል፥ የወንድሜ የብንያምም ዓይኖች አይተዋል።

13፤ ለአባቴም በግብፅ ምድር ያለኝን ክብሬን ሁሉ ያያችሁትንም ሁሉ ንገሩት፤ አባቴንም ወደዚህ ፈጥናችሁ አምጡት።

14፤ የወንድሙን የብንያምንም አንገት አቅፎ አለቀሰ፤ ብንያምም በአንገቱ ላይ አለቀሰ።

15፤ ወንድሞቹን ሁሉ ሳማቸው፥ በእነርሱም ላይ አለቀሰ፤ ከዚያም በኋላ ወንድሞቹ ከእርሱ ጋር ተጫወቱ።

16፤ በፈርዖንም ቤት። የዮሴፍ ወንድሞች መጡ ተብሎ ወሬ ተሰማ፤ በዚያውም ፈርዖንና ሎላልቱ ደስ ተሰኙበት።

17፤ ፈርዖንም ዮሴፍን አለው። ለወንድሞችህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው። ይህን አድርጉ፤ ከብቶቻችሁን ጭናችሁ ወደ ከነዓን ምድር ሂዱ፤

18፤ አባታችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ይዛችሁም ወደ እኔ ኑ፤ እኔም የግብፅን ምድር በረከት ሁሉ እሰጣችኋለሁ፥ የምድሪቱንም ስብ ትበላላችሁ።

19፤ አንተም ወንድሞችህን። እንዲህ አድርጉ በላቸው፤ ከግብፅ ምድር ለሕፃናቶቻችሁ ለሴቶቻችሁም ሰረገሎችን ውሰዱ፥ አባታችሁንም ይዛችሁ ኑ፤

20፤ ለዕቃችሁም ሁሉ አታስቡ፥ የግብፅ በረከት ሁሉ ለእናንተ ነውና።

21፤ የእስራኤል ልጆችም እንደዚሁ አደረጉ፤ ዮሴፍም በፈርዖን ትእዛዝ ሰረገሎችንና ለመንገድ ስንቅ ሰጣቸው፤

22፤ ለሁሉም ሁለት ሁለት መለወጫ ልብስ ሰጣቸው፥ ለብንያም ግን ሦስት መቶ ብርና አምስት መለወጫ ልብስ ሰጠው።

23፤ ለአባቱም እንደዚሁ ሰደደ፥ የግብፅን በረከት የተሸከሙ አሥር አህዮችን፥ ደግሞም በመንገድ ለአባቱ ስንቅ ስንዴና እንጀራ የተሸከሙ አሥር ሴቶች አህዮችን።

24፤ ዮሴፍም ወንድሞቹን አሰናበታቸው፥ እንዲህም አላቸው። በመንገድ እርስ በርሳችሁ አትጣሉ።

25፤ እነርሱም ሄዱ፥ ከግብፅ አገርም ወጡ፥ ወደ ከነዓንም ምድር ከአባታቸው ከያዕቆብ ዘንድ ደረሱ።

26፤ እንዲህም ብለው ነገሩት። ዮሴፍ ገና በሕይወቱ ነው፥ እርሱም በግብፅ ምድር ሁሉ ላይ ገዥ ሆኖአል። ያዕቆብም ልቡ ደነገጠ፥ አላመናቸውም ነበርና።

27፤ እነርሱም ዮሴፍ የነገራቸውን ነገር ሁሉ ነገሩት፤ እርሱን ያነሡት ዘንድ ዮሴፍ የሰደዳቸውን ሰረገሎች ባየ ጊዜ የአባታቸው የያዕቆብ የነፍሱ ሕይወት ታደሰች።

28፤ እስራኤልም። ልጄ ዮሴፍ ገና በሕይወት ከሆነ ይበቃኛል፤ ሳልሞት እንዳየው እሄዳለሁ አለ።

ኦሪት ዘፍጥረት ፤ ምዕራፍ 44

1፤ ዮሴፍም የቤቱን አዛዥ እንዲህ ብሎ አዘዘ። ዓይበታቸው የሚያነሣውን ያህል እህል ሙላላቸው፥ የሁሉንም ብር በየዓይበታቸው አፍ ጨምረው፤

2፤ በታናሹም ዓይበት አፍ የብሩን ጽዋዬንና የእህሉን ዋጋ ጨምረው። እርሱም ዮሴፍ እንዳለው አደረገ።

3፤ ነግህ በሆነ ጊዜም ሰዎቹ አህዮቻቸውን ይዘው ይሄዱ ዘንድ ተሰናበቱ።

4፤ ከከተማይቱም ወጥተው ገና ሳይርቁ ዮሴፍ ለቤቱ አዛዥ እንዲህ አለ። ተነሥተህ ሰዎቹን ተከተላቸው፤ በደረስህባቸውም ጊዜ እንዲህ በላቸው። በመልካሙ ፋንታ ስለ ምን ክፉን መለሳችሁ?

5፤ ጌታዬ የሚጠጣበት ምሥጢርንም የሚያውቅበት ጽዋ አይደለምን? ባደረጋችሁት ነገር በደላችሁ።

6፤ እርሱም ደርሰባቸው ይህንም ቃል ነገራቸው።

7፤ እነርሱም አሉት። ጌታዬ እንደዚህ ያለውን ቃል ለምን ይናገራል? ባሪያዎችህ ይህን ነገር የሚያደርጉ አይደሉም።

8፤ እነሆ፥ በዓይበታችን አፍ ያገኘነውን ብር ይዘን ከከነዓን አገር ወደ አንተ ተመልሰናል፤ ከጌታህ ቤት ወርቅ ወይስ ብር እንዴት እንሰርቃለን?

9፤ ከባሪያዎችህ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ይሙት፤ እኛም ደግሞ ለጌታችን ባሪያዎች እንሁን።

10፤ እርሱም አለ። አሁንም እንዲሁ እንደ ነገራችሁ ይሁን፤ ጽዋው የተገኘበት እርሱ ለእኔ ባሪያ ይሁነኝ፥ እናንተም ንጹሐን ትሆናላችሁ።

11፤ እየራሳቸውም ፈጥነው ዓይበታቸውን ወደ ምድር አወረዱ፥ እየራሳቸውም ዓይበታቸውን ፈቱ።

12፤ እርሱም ከታላቁ ጀምሮ እስከ ታናሹ ድረስ በረበራቸው፥ ጽዋውንም በብንያም ዓይበት ውስጥ አገኘው።

13፤ ልብሳቸውንም ቀደዱ፥ ዓይበታቸውንም በየአህዮቻቸው ጭነው ወደ ከተማይቱ ተመለሱ።

14፤ ይሁዳም ከወንድሞቹ ጋር ወደ ዮሴፍ ገባ፥ እርሱም ገና ከዚያው ነበረ፤ በፊቱም በምድር ላይ ወደቁ።

15፤ ዮሴፍም። ይህ ያደረጋችሁት ነገር ምንድር ነው? እንደ እኔ ያለ ሰው ምሥጢርን እንዲያውቅ አታውቁምን? አላቸው።

16፤ ይሁዳም አለ። ለጌታዬ ምን እንመልሳለን? ምንስ እንናገራለን? ወይስ በምን እንነጻለን? እግዚአብሔር የባሪያዎችህን ኃጢአት ገለጠ፤ እነሆ፥ እኛም ጽዋው ከእርሱ ዘንድ የተገኘበቱም ደግሞ ለጌታዬ ባሪያዎቹ ነን።

17፤ እርሱም እላቸው። ይህን አደርግ ዘንድ አይሆንልኝም፤ ጽዋው የተገኘበቱ ሰው እርሱ ባሪያ ይሁነኝ፤ እናንተም ወደ አባታችሁ በደኅና ውጡ።

18፤ ይሁዳም ወደ እርሱ ቀረበ እንዲህም አለ። ጌታዬ ሆይ፥ እኔ ባርያህ በጌታዬ ጆሮ አንዲት ቃልን እንድናገር እለምናለሁ፤ እኔንም ባሪያህን አትቆጣኝ፤ አንተ እንደ ፈርዖን ነህና።

19፤ ጌታዬ ባሪያዎቹን። አባት አላችሁን ወይስ ወንድም? ብሎ ጠየቀ።

20፤ እኛም ለጌታዬ እንዲህ አልነ። ሸማግሌ አባት አለን፥ በሽምግልናው የወለደውም ታናሽ ብላቴና አለ፤ ወንድሙም ሞተ፥ ከእናቱም እርሱ ብቻውን ቀረ፥ አባቱም ይወድደዋል።

21፤ አንተም ለባሪያዎችህ። ወደ እኔ አምጡት፥ እኔም አየዋለሁ አልህ።

22፤ ጌታዬንም። ብላቴናው አባቱን መተው አይሆንለትም፤ የተወው እንደ ሆነ አባቱ ይሞታልና አልነው።

23፤ ባርያዎችህንም። ታናሽ ወንድማችሁ ከእናንተ ጋር ካልመጣ ዳግመኛ ፊቴን አታዩም አልኽን።

24፤ ወደ ባርያህ ወደ አባታችን በተመለስን ጊዜም የጌታዬን ቃል ነገርነው።

25፤ አባታችንም። ተመልሳችሁ ጥቂት እህል ሸምቱልን አለ።

26፤ እኛም አልነው። እንሄድ ዘንድ አይሆንልንም፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ይወርድ እንደ ሆነ እኛም እንወርዳለን፤ ታናሹ ወንድማችን ከእኛ ጋር ከሌለ የዚያን ሰው ፊት ማየት አይቻለንምና።

27፤ ባሪያህ አባቴም እንዲህ አለን። ሚስቴ ሁለት ወንዶች ልጆችን እንደ ወለደችልኝ እናንተ ታውቃላችሁ፤

28፤ አንዱም ከእኔ ወጣ። አውሬ በላው አላችሁኝ፥ እስከ ዛሬም አላየሁትም፤

29፤ ይህንም ከእኔ ለይታችሁ ደግሞ ብትወስዱት ክፋም ቢያገኘው፥ ሽበቴን በኅዘን ወደ መቃብር ታወርዱታላችሁ።

30፤ አሁንም እኔ ወደ አባቴ ወደ ባሪያህ ብሄድ፥ ብላቴናውም ከእኛ ጋር ከሌለ፥ ነፍሱ በብላቴናው ነፍስ ታስራለችና ብላቴናው ከእኛ ጋር እንደሌለ ባየ ጊዜ ይሞታል፤

31፤ ባሪያዎችህም የባሪያህን የአባታችንን ሽበት በኅዘን ወደ መቃብር ያወርዳሉ።

32፤ እኔ ባሪያህ በአባቴ ዘንድ ስለ ብላቴናው እንዲህ ብዬ ተውሼአለሁና። እርሱንስ ወደ አንተ ባላመጣው በአባቴ ዘንድ በዘመናት ሁሉ ኃጢአተኛ እሆናለሁ።

33፤ ስለዚህም እኔ ባሪያህ በጌታዬ ዘንድ ባሪያ ሆኜ በብላቴናው ፋንታ ልቀመጥ፤ ብላቴናውም ከወንድሞቹ ጋር ይውጣ።

34፤ አለዚያም ብላቴናው ከእኔ ጋር ከሌለ ወደ አባቴ እንዴት እወጣለሁ? አባቴን የሚያገኘውን መከራ እንዳላይ።